የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ ት/ቤቶች 75ቱ ተጠናቀቁ

By Melaku Gedif

April 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 75 የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ÷ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ በመልሶ መቋቋም ጽ/ቤትና በክልሉ መንግስት በተመደበ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመገንባት ላይ ካሉ 50 የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች 42ቱ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን አመልክተዋል።

እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ እየተገነቡ ካሉ 45 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 33ቱ መጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት፡፡

በትምህርት ቤቶች ያለውን የክፍል ጥበት ችግር ለማቃለል የተገነቡ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እንዳሉም ተጠቅሷል።

የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶቹ ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የአስተዳደር፣ የቤተ ሙከራ፣ የቤተ መፃህፍትና የአይሲቲ ህንፃዎችና ክፍሎችን አካተው መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኙ ቀሪ ት/ ቤቶችን በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።