ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከዩኤንኤድስ ሪጅናል ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከዩኤንኤድስ ሪጅናል ዳይሬክተር አን ሙዞኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ለኤች አይ ቪ ተጋላጭነት የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመከላከል አኳያ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ መክረዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፥ በሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ለማስከበር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፣ የልጃገረዶች ትምህርትና የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ተደራሽነትን ማስፋፋት የኤችአይቪ ስርጭትን ለመግታት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
ከዚህ ረገድ የስርዓተ ጾታ ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱ እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያግዝ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ተነድፎ በስራ ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል፡፡
ጥቃትን ጨምሮ በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ እና መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ያለመ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አን ሙዞኒ በበኩላቸው፥ዩኤንኤድስ ስርዓተ ጾታ ከኤችአይቪ ጋር ያለውን ትስስርና ስርጭቱን በመግታት ረገድ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በጥናት መለየቱን አንስተዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከወረዳ ጀምሮ ትኩረት በመስጠት መሰራት እንዳለበት ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
የታዳጊ ህጻናትን፣ የወጣት ሴቶችንና የወጣቶችን በቫይረሱ መያዝ ለመከላከል ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን በማቋቋምና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊከናወኑ የሚገባቸውን መስኮች በጋራ በመለየት ወደ ስራ ለመግባት ስምምነት ላይ መደረሱም ተጠቁሟል፡፡