Fana: At a Speed of Life!

ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በጤናው ዘርፍ ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራ ልዑክ በቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ማርክ ሱዝማን ከተመራ ልዑክ ጋር ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጤና አጀንዳዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ÷ በተሰሩ በርካታ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ እየጨመረ የመጣውን የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ለማርካት ግን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ብለዋል።

ከክልል ክልል እንዲሁም በገጠርና በከተማ ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት እንደሚለያይም ነው ያስረዱት፡፡

የሰው ሃይልን ማጠናከር፣ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎትን ማሳደግ፣ ዲጂታል ጤና፣ ስርዓተ ምግብና ዘላቂነት ያለው የጤና ፋይናንስ የዘርፉ ቀዳሚ አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዓለም አቀፋዊ አውድ ሲቀየር በዚያው ልክ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ ፋውንዴሽኑ የጤናው ዘርፍ እንዲጠናከር ለረጅም ጊዜ ሳያቋርጥ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

በቀጣይም አጋርነቱን አጠናክረው እንዲቀጥል መጠየቃቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ማርክ ሱዝማን በበኩላቸው የበጀት እጥረትን በመቋቋም አገልግሎቶችን ለማስቀጠል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀው÷ በቀጣይም አጋርነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.