የሀገር ውስጥ ዜና

የልማት ተነሺዎች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ተደርጓል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Tamrat Bishaw

April 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅርብ ክትትል በማድረግ የልማት ተነሺዎች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ተደርጓል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዋን የልማት ኮሪደርን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ለንግድ ቤቶች እና ለግል ባለይዞታዎች ምትክ መሬትና የካሣ ክፍያዎችን መፈጸም ተችሏል።

እንዲሁም የልማት ተነሺዎች ወደ ተዘጋጀላቸው የመኖሪያና የመስሪያ ቦታ የሚያጓጉዝ ትራንስፖርት ማዘጋጀት፣ በገቡበት አካባቢ ልዩ አቀባበል ማድረግ፣ በአብዛኛው ማህበራዊ ትስስራቸው ተጠብቆ የማዘዋወር ሥራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት ስሜት ተከናውኗል ብለዋል።

ግልፅና ዝርዝር የማስፈጸሚያ እቅድ በማዘጋጀት የዲዛይን ዝግጅት፣ በጀትና ለልማት ተነሺዎች መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ መስሪያ ቦታና ምትክ መሬት የማዘጋጀት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ከመኖሪያ እና መስሪያ ቦታቸዉ የሚነሱ የልማት ተነሺዎችን መረጃ ማደራጀት፣ ተነሺዎችን ማወያየት፣ በምርጫቸዉ መሰረት በተቀላጠፈ አግባብ የሚስተናገዱበት ስርዓትና የሚያጋጥሙ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት ተዘርግቶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

የልማት ተነሺዎች የገቡባቸዉ የመኖሪያ ቤቶች የመንገድ፣ የመብራት፣ የውሃና ፍሳሽ መሠረተ ልማቶች የተሟላላቸው ስለመሆኑና የቅርብ ክትትል በማድረግ ተነሺዎች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው መደረጉን እንደገለጹ የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

የከተማው ከፍተኛ አመራር የመኖሪያ ቦታዎችን ሁኔታ እና የልማት ተነሺዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመጎብኘትና አገልግሎት ስለመሟላቱና ጉድለቶችም ካሉ ለማረም የሚያስችል ጉብኝት በሁሉም ሳይቶች ላይ በተደጋጋሚ ማድረጉንም ከንቲባዋ ጠቁመዋል።