ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባርና ንቅናቄ ይፋ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባርና ንቅናቄ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል።
የማኅበረሰቡን የጽዳት ባህል ክብርን የጠበቀ ለማድረግ የተወጠነው ይህ ተነሣሽነት፣ መጸዳጃ ቤቶችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ መገንባት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።
ይህንንም ለማሳየት አንድ ናሙና ተገንብቶ እንደ ማሳያ በመዲናዋ መቀመጡም ተመላክቷል፡፡
“ጽዱ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ተነሣሽነት “ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ሀሳብ በገንዘብ ወይም በዓይነት የኅብረተሰብ ደጋፍ እንደሚሻም ነው የተገለጸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንቅናቄውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ፥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ከተሰጠባቸው ነገሮች አንዱ ጽዱ እና አረንጓዴ ከባቢ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
“ክብር ያለው የንጽህና ባህል መፍጠር ይኖርብናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተገቢው ቦታ ክብርን ጠብቆ መጸዳዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ለዚህ ደግሞ ሥርዓት ማበጀት እና የመጸዳጃ ቦታ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በማስተማር እና ሕግ በማስከበር ሥርዓቱን ማሳደግ እንዲሁም የመጸዳጃ ቦታን መገንባት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ንቅናቄው የመጸዳጃ ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ክብርን ጠብቆ የመጸዳዳት ባህልን ማዳበር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ንቅናቄው የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ጤናን ለመጠበቅ እንደሚያግዝም መግለጻቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
“በዚህ መልካም ተግባር ላይ ኢትዮጵያውያን ከተማችንን ጽዱ፤ አረንጓዴ እና ውብ ለማድረግ ከጎናችን እንደምትቆሙ ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል።
በከተማዋ በርከት ያሉ የመጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት ኢትዮጵያውያን በገንዘብ አልያም በመገንባት እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል።