ስኬታማ የፓለቲካና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማስቀጠል ክልሎች የእርስ በርስ የፓለቲካ ሥራዎችን ማጠናከር አለባቸው – ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በአሶሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በአፈፃፀም መድረኩ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ÷መድረኩ ባለፉት 9 ወራት በዘርፉ ከተቀመጠው ዕቅድ አኳያ አፈፃፀሙን በጋራ በመገምገም ያለበትን ደረጃ ለመለየት ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ የተግባራትን ስኬታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም ውጤታማ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ስኬታማ የፓለቲካና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማስቀጠል ክልሎች የእርስ በርስ የፓለቲካ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የግምገማው መድረኩ የ2017 ዓ.ም የዘርፉ የርብርብ ማዕከል ተለይቶ አቅጣጫ እንደሚቀመጥበት ሃላፊው መናገራቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷የብልፅግና ፓርቲ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሁለንተናዊ ለውጦችን እውን ማድረግ በሚያስችል መልኩ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ብልፅግና በአመለካከትና በተግባር የተዋሃደ አመራርን በመፍጠር ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ስርዓት ለመገንባት ዋና አላማው አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ ሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር የዘርፉ የ9 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ተጠቁሟል፡፡