ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ያሸነፉት የሰላም የኖቤል ሽልማት ለሰላም ባሳዩት ቁርጠኝነት የተገኘ ነው – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተርበ ዐቢይ አህመድ ያሸነፉት የሰላም የኖቤል ሽልማት ለሰላም ባሳዩት ቁርጠኝነት የተገኘ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኖቤል ሽልማት መቀበል አስመልክቶ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዝግጅት ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ባሳዩት ቁርጠኝነት የተገኘ እና እውቅናውም የመላው ኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሰላም ዘብ እንዲቆምና በሚችለው ሙያ ሁሉ ሃገሩን እንዲደግፍ አሳስበዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፥ የኖቤል ሽልማቱ እስካሁን ከተመዘገቡ ድሎች ባሻገር በቀጣይ ከዚህ ለላቀ ስኬት ለመስራት የሚያግዝ ስንቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በዝግጅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የውሀ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ አምባሳደር ፍፁም አረጋ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች፣ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አመራሮች፣ የማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መረጃው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው፤