ለሰላም ኖቤል ተሸላሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ነገ አቀባበል ስነ ስርዓት ይደረጋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ለሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በነገው እለት የአቀባበል ስነ ስርዓት እንደሚደረግ ተገለፀ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለት በኖርዌይ ኦስሎ ተገኝተው የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን መቀበላቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ነገ ከኖርዌይ ኦስሎ ሲመለሱ የጀግና አቀባበል ስነ ስርዓት ይደረግላቸዋል።
የአቀባበል ስነ ስርዓቱም በነገው እለት ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ብሄራዊ ቤተ መንግስት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
የአቀባበል ስነ ስርዓቱንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑን ገልፀዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች እና የማርሽ ባንዶች እና የሰራዊት አባላት ለአቀባበል ስነ ስርዓቱ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነም ነው ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የተናገሩት።
ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሚደረገው የጀግና አቀባበል ፕሮግራም ላይም ሁሉም የከተማዋ እና የአዲስ አበባ ዙሪያ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።