የሀገር ውስጥ ዜና

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሸሸና የተመዘበረ ሃብትን ለማስመለስ በጋራ እንዲሰሩ ተጠየቀ

By Mikias Ayele

May 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር ከሀገር የሸሸና የተመዘበረ ሃብትን ለማስመለስ እንዲሁም በተያያዥ ወንጀሎች ላይ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሸሸ እና የተመዘበረ ሃብትን ለማስመለስ እንዲሁም በተያያዥ ወንጀሎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ጥምረት መስርተዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ÷ የሙስና ወንጀል ለኢትዮጵያ እድገት ተፅዕኖ እየሳደረ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የሆነና የሀገራችን ብሎም ዓለም አቀፋዊ ችግር የሆነውን የሙስና ወንጀል ለመቅረፍ በቅንጅት መስራት ካልቻልን ተፅዕኖው የጎላ ነው ብለዋል።

ወንጀሉን ለመከላከል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር ከሀገር የሸሸና የተመዘበረ ሃብትን እንዲሁም ተያያዥ ወንጀሎችን ለመከላከል ስምምነት መፍጠራቸው ጠቃሚ  መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሀገር ውስጥ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን  የገለፁት ም/ኮሚሽነሩ÷በቀጣይ ከሀገራትና ተቋማት ጋር ተሞክሮዎችንና መረጃዎችን የመለዋወጥ  ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የፀረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

መድረኩ ነገ ቀጥሎ ሲካሄድ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርን ጨምሮ የሌሎች ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡