በዓለም የአቪዬሽን ድርጅት ሲንፖዚየም ኢትዮጵያ በርካታ ፋይዳዎች ማግኘቷ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም የአቪዬሽን ድርጅት ሉላዊ አፈፃፀም ድጋፍ ሲንፖዚየም ላይ ኢትዮጵያ ባደረገችው ተሳትፎ በርካታ ፋይዳዎች ማግኘቷን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ባላፉት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዓለም የአቪዬሽን ድርጅት ሉላዊ የአፈፃፀም ድጋፍ ሲንፖዚየም መጠናቀቁን ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፉ ለቱሪዝም ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ ተጨባጭ ተሞክሮዎችን ዋቢ በማድረግ ልምዷን ማካፈል መቻሏንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ተሞክሯዋን በማየትም በርካታ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ዘርፍ በፋይናንስና በቴክኒክ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡
ለአየር ንብረት ተስማሚ የአውሮፕላን ነዳጅ ለማምረት የተጀመረውን እንቅስቃሴ በተመለከተም በኢትዮጵያ በኩል ያለውን እንቅስቃሴ በመድረኩ ማሳወቅ መቻላቸውን ነው የገለጹት፡፡