የሀገር ውስጥ ዜና

የትንሳኤ በዓል አብሮነታችን የሚጠናከርበት ሊሆን ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Tamrat Bishaw

May 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በነገው ዕለት የሚከበረው የትንሳኤ በዓል አብሮነታችን የሚጠናከርበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ ለክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ትንሳኤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች እስከሞት ድረስ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ፍቅር ያሳየበት እና ለበደሉት ሁሉ ምኅረት የሰጠበት መሆኑን አስታውሰው÷ ሞትንም ድል ያደረገበት መታሰቢያ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እኛም እርስ በርሳችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም ሰው በመውደድ፣ በይቅርታ፣ በምኅረትና በመረዳዳት እንድንኖር ፈጣሪ ይርዳን ሲሉም ነው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የገለጹት፡፡

በዓሉ የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የምኅረት፣ የመረዳዳት፣ የደስታ እና አብሮነታችን የሚጠናከርበት ይሁን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡