Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል ባላቸው ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቅሬታ ምንጭ ሆነዋል ባላቸው ከ20 በላይ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ።

በ2011 ዓ.ም ከአስቸኳይ ጥገና፣ ከኃይል መቆራረጥና አዳዲስ ጥያቄዎች፣ ከቅድመ ቆጣሪ ክፍያ መስተንግዶ፣ ከንብረት አያያዝና አጠቃቀም እና ከሌሎች ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ 13 ሺህ 441 ደንበኞች ቅሬታ ቀርበው ምላሽ እንደተሰጣቸው የክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማተቤ ዓለሙ ገልጸዋል።

ከሠራተኞች የስነ ምግባር ግድፈት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንና ለውጤታማነቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ጣሰው በበኩላቸው፥ ከቀረቡት ቅሬታዎች መካከል በሠራተኞች ችግር የተፈጠሩ እና ተጠያቂ የሚያደርጉ እንደሚገኙበት አንስተዋል።

በዚህም ከህብረተሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎች፣ በተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች በሚደረጉ ክትትሎችና የኦዲት ግኝቶች መነሻነት ጥፋት በፈጸሙ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ከተቋሙ አሠራርና ደንብ በማፈንገጥ የሥነ ምግባር ጥሰት የፈጸሙ ሠራተኞች፥ በተለያየ ደረጃ ቅጣት እንደተላለፈባቸው ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ለ10 ሠራተኞች የጽሑፍ እና የቃል ማስጠንቀቂያ፣ ስምንት ሠራተኞች በገንዘብ እንዲሁም ሦስት ሠራተኞች ደግሞ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉንና የአንድ ሠራተኛ የስነ ምግባር ጉዳይም እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ መስሪያ ቤቱ በ2011 ዓ.ም በ21 ሠራተኞች ላይ የስነ ምግባር እርምጃ የተወሰደና ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር የነበረበትን ጊዜያዊ ቅጥር የማስቆም ውሳኔ ተላልፏል ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.