Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በዓለም አቀፍ የሮቦፌስት ውድድር ላይ እየተሳተፉ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በዓለም አቀፍ የሮቦፌስት ውድድር ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ አቅንተው በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ተወዳዳሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ፣ አብርሆት ላይብራሪ ከአቦጊዳ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ማዕከል ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማወዳደር በገቡት ስምምነት መሰረት መሆኑም ተገልጿል።

አሜሪካ በሚገኘው የሚችጋን ላውረንስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሚካሄደው ውድድር 23 ታዳጊዎች ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ ዘርፎች ለውድድር እየቀረቡ እንደሆነ ታውቋል።

ከግንቦት 2 እስከ 5 ቀን 2016 በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች የሚያሸንፉ ከሆነ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ነፃ የትምህርት እድል እንደሚያገኙ ተገልጿል።

የሮቦፌስት ውድድር በሎረንስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአሜሪካን ሚችጋን ክፍለ ግዛት ውስጥ የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ውድድር ሲሆን ዋነኛ አላማውም ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማበልፀግ ዝንባሌው ያላቸውን ታዳጊ ህፃናት በዘርፉ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር ነው እንደሆነ ተገልጿል።

ውድድሩንና ተወዳዳሪዎችን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የህግ ባለሙያው አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) የመደመር ትውልድ ልጆች ሀገራቸውን የሚያስጠራ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ እምነታቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.