የሕግ ማስከበሩና የሰብዓዊ መብት አያያዙ በመርህ ላይ የተመሠረተ ነው – መርማሪ ቦርዱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕግ ማስከበሩ እና የሰብዓዊ መብት አያያዙ በመርህ ላይ የተመሠረተ ነው ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የቦርዱ አባላት በአማራ ክልል በሰሜን ምዕራብ ኮማንድፖስት ሥር በጎንደር ከተማ በሚገኘው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል፡፡
በኮማንድ ፖስቱ እየተተገበረ ያለው የሕግ ማስከበር በዜጎች ላይ የመብት ጥሰት እንዳይደርስ በጥንቃቄ መተግበሩ በሕዝቡ ቅቡልነት እንዲኖረው ማድረጉን የገለጸው ቦርዱ፤ የሕግ ማስከበር ሥራው ሰላም እያደገ እንዲሄድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጿል።
የቦርዱ አባላት በምልከታውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የተያዙ ተጠርጣሪዎች በምህረት እና የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ መደበኛ ሥራዎቻቸው እንዲመለሱ በመደረጉ የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር በእጅጉ እንደቀነሰ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ የተለያዩ መደበኛ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም የኮማድፓስቱ የሥራ ኀላፊዎች ለቦርዱ አባላት መግለጻቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመልክቷል።
በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ትኩረትን ወደ ልማት ማዞር እንደሚገባም መርማሪ ቦርዱ አስገንዝቧል።