ቃኘው ሻለቃ በኮሪያ የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው – አምባሳደር ታዬ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈፀመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ወደ ኮርያ የዘመተችበትን 73ኛ ዓመት አክብሯል፡፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ÷ በኮርያ ሰላም ማስከበር ላይ ለተሳተፉ ዘማቾች ክብር መስጠትና ማመስገን ብሎም ታሪካቸውን መሰነድ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለኮርያ ሰላም መረጋገጥ ያበረከተችው አስተዋፅኦ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከሩን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በወቅቱ ያበረከተችው ሚና የሀገራችንን ህዝቦች በጎነት ያሳየ ነበር ሲሉ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሰላም የከፈለችው ዋጋ የማይዘነጋ መሆኑን ገልፀው፤ ለተደረገው ወታደራዊ ድጋፍ አመስግነዋል።
የቃኘው ሻለቃ ጦር የከፈለው ዋጋ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮርያ መካካል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር መሠረት መጣሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ኮሪያ የዘመቱበትን 73ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አክብረናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡