ሶማሌ ክልል 362 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች በብድር ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ለአርሶ አደሮች በብድር የሚሰጣቸውን 362 በላይ ትራክተሮች ጅግጅጋ ማስገባቱን አስታወቀ፡፡
ይህም ቢሮው ላለፉት አራት ዓመታት ሲያካሂድ የቆየው የግብርና ምርትና ምርታማነት የማሳደግ መርሐ-ግብር አካል ነው ተብሏል፡፡
ዘመናዊ ትራክተሮችን በብድር የሚወስዱ አርሶ አደሮች 50 በመቶ ቅድሚያ የሚከፍሉ ሲሆን÷ ቀሪውን 50 በመቶ ደግሞ በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚከፍሉ ተገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ በብድር የሚጠቀምባቸው ትራክተሮች ክልሉ ምርትን ለማሳደግና በምግብ እራስን ለመቻል ለሚያደርገው ጥረትን ትልቅ ሚና እንዳላቸውም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።