በኦሮሚያ ክልል በህብረተሰቡ ድጋፍና በመንግስት የተገዙ 234 አምቡላንሶችን የክልል መንግስት ተረከበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በህብረተሰቡ ድጋፍና በመንግስት የተገዙ 234 አምቡላንሶችን የክልሉ መንግስት ከጤና ሚኒስቴር ተረከበ።
በርክክቡ ወቅት አምቡላንሶቹ በፌደራል፣ በክልል መንግስት እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገዙ መሆኑ ታውቋል።
አምቡላንሶቹ ከቀረጥ ነፃ 284 ሚሊየን 778 ሺህ ብር ወጪ እንደተደረገባቸውም ተገልጿል።
በሚኒስቴሩ የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክቶሬት አቶ እስክንድር ላቀው የአምቡለንሶቹን ቁልፎች ለኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንግስቱ በቀለ አስረክበዋል፡፡
አቶ እስክንድር በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት የጤና ሚኒስቴር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ 3 ሺህ 10 አምቡላንሶችን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ተገዝተው ለክልሎች፣ ለከተማ አስተዳደሮች እና ለዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች እንዲሰራጩ አድርጓል፡፡
አምቡላንሶቹ የጤና ሚኒስቴር እና ክልሎች በደረሱበት ስምምነት መሠረት በመንግስትና በህብረተሰቡ ድጋፍ የተገዙ መሆኑን አስታውሰው ክልሎችም ሆኑ የከተማ አስተዳደሮችና የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች የአምቡላንሶችን ግማሽ ወጪ ገቢ ካደረጉ በኋላ ርክክቡ ልክ እንደ ዛሬው ካሁን በፊትም በሁለት ዙሮች ከሌሎች ጋር ተፈጽሟል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንግስቱ በቀለ በበኩላቸው የተረከቡትን አምቡላንሶች ክልሉ ለተለያዩ የጤና አገልግሎቶችና የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ተግባር እንደሚያውላቸው ገልፀው ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡