Fana: At a Speed of Life!

የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ 95 በመቶ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እየተገነባ የሚገኘው የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ 95 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

በ2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የነቀምቴ ኡኬ አውሮፕላን ማረፊያ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ወንድሙ ዋጋው(ኢ/ር) ተናግረዋል፡፡

በብዙ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ለ2 ዓመታት ግንባታው ተቋርጦ የቆዬ ቢሆንም አሁን ላይ 95 በመቶ መጠናቀቁን ነው የገለጹት።

በ220 ሄክታር ላይ ግንባታው እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ፥ 2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የአውሮፕላን መንደርደሪያና 60 ሜትር ስፋት ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ በሁሉም ዘርፎች ሀገር በቀል ሙያተኞችን ብቻ የሚጠቀም በመሆኑ ለአካባቢው ማህበረሰብ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡

ካሉት 275 ሰራተኞች መካከል 218 ለሚሆኑት የአካባቢው ተወላጆች በተሻለ ገቢ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

አካባቢው በርካታ የግብርና ምርቶችና የንግድ ሥራዎች በስፋት የሚከናወኑበት በመሆኑ ይህ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀሪ ተግባራትን ያለ ዕረፍት በማጠናቀቅ በተያዘው ዓመት ለማስረከብ እየተጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለስኬቱ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ ባለ ድርሻ አካላትና የመከላከያ ሰራዊት ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.