ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚገነባው የካሊድ ዲጆ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1 ነጥብ 19 ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው የካሊድ ዲጆ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሃሪ እና የደቡብ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ ቱሮ ተፈራርመውታል።
ፕሮጀክቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በስልጤ ዞን አስተዳደር በዱለቻ ወረዳ በዲጆ ወንዝ ላይ የሚገነባ ነው።
ግንባታው ሲጠናቀቅም 1 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፥ ከ2 ሺህ 200 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የካሊድ ዲጆ ግድብ 1 ሺህ 731 ሜትር ርዝመት እና 25 ነጥብ 5 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን በአለትና በውስጥ በኩል በሸክላ አፈር የሚገነባ ነው።
ግንባታው በደቡብ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የሚካሄድ መሆኑን ከመስኖ ልማት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።