Fana: At a Speed of Life!

40 የእርሻ ትራክተሮች ርክክብ በባህር ዳር ከተማ ተካሄደ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልሉ ግብርና ቢሮ ከኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ያቀረባቸውን 40 የእርሻ ትራክተሮች ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ርክክብ አካሂዷል።

በአማራ ክልል የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የእርሻ ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት÷ ግብርናውን ለማዘመንና የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በዛሬው ዕለትም 286 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው 40 ትራክተሮችን በደቡብ ጎንደር እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የቁልፍ ርክክብ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ የዛሬዎቹን ጨምሮ ባለፉት 10 ወራት 148 የእርሻ ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸውን ገልፀዋል።

የተሰራጩት የእርሻ ትራክተሮች አርሶ አደሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ፋይዳቸው የጎላ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ እርቅይሁን ገላው በበኩላቸው÷ኮርፖሬሽኑ የእርሻ ትራክተሮች ከማቅረብ በተጨማሪ በየአካባቢው የመለዋወጫና የጥገና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.