Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) አመሠገነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምሥጋና አቅርበዋል።

የምሥጋና መልዕክቱ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተፈጥሮ ፀጋ የታደለችውን እና የተፈጥሮ ውበቷን የበለጠ ፍንትው አድርጎ በማውጣት የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን የወርቃማ ዕድል ባለቤት በሆነችው ጎርጎራ፤ ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ስለሀገር ክብር እና ስለሕዝብ ጥቅም በዝርዝር ከመከሩ በኋላ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም የሁሉም ክልል ርዕሳነ-መሥተዳድሮች እና ሚኒስትሮች በተገኙበት በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ በመገኘት በዓለማችን ትልቁ ወንዝ በሆነው ዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ መርቀው ሥራ አስጀምረውልናል።

ለዚህ በጎ ተግባርዎ፤ በታላቁ የክልላችን ሕዝብ እና በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ስም ምሥጋናዬን በታላቅ አክብሮት አቀርባለሁ።

በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለክልላችን ሁለንናዊ ልማት እና ሰላም መረጋገጥ ይበጅ ዘንድ በታላቁ የዓባይ ድልድይ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝታችሁ የአበረታታችሁን ርዕሳነ-መሥተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎች የፌደራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ስለአደረጋችሁልን ሁሉ እጅግ እናመሠግናለን።

እጅግ ለተከበራችሁ እና እንግዳ ተቀባይነት መገለጫችሁ ለሆነው የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በሙሉ በፀረ-ሰላም ኃይሎች የነበረባችሁን ጫና ከምንም ሳትቆጥሩ በምረቃ ቦታው በመገኘት እና እንግዶችን በመቀበል ላሳያችሁት ፍቅር እና አክብሮት በራሴ እና በክልላችን መንግሥት ስም ከፍ ያለ ምሥጋናየን አቀርባለሁ።

የተከበራችሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፤ እንደዚህ ዓይነቶቹ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ ዛሬ እንዳሳያችሁት አንድነት እና ኅብረት ሁሉ ከተማችን የበለጠ ሰላሟና ልማቷ እንዲረጋገጥ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ እንድትሠሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

በጫካ ለምትገኙ ወንድሞቻችንም በእውነት ከክልላችን ሕዝብ ጥቅም እና ክብር ውጭ ሌላ ስውር አጀንዳ ከሌላችሁ በስተቀር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባቀረቡላችሁ ጥሪ መሠረት ችግሮቻችንን በውይይት እና በድርድር እንድንፈታና ሕዝባችንም እፎይታ እንዲያገኝ በድጋሜ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

በመጨረሻም መላ የክልላችን ሕዝብ በክልላችን የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም የበለጠ ስር እንዲሰድ እና የልማት ሥራዎች ሳይስተጓጎሉ የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የማይተካ ሚናህን እንድትወጣ በድጋሜ ጥሪየን በአክብሮት አቀርባለሁ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.