ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በጎንደር የሚገኙ ሶስት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መመሪያ ሰጡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጎንደር የሚገኙ ሶስት እጅግ አስፈላጊ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የፕሮጀክቶቹ አስተዳደር ማሻሻያ እንዲደረግ መመሪያ ሰጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷”በሳምንቱ መጨረሻ በአማራ ክልል ከነበረን ቆይታ ተመልሰን ከከፍተኛ የፌደራል የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጎንደር የሚገኙ ሶስት እጅግ አስፈላጊ ፕሮጀክቶችን የሥራ አፈፃፀም በመገምገም የሚጠናቀቁበትን መንገድ አስቀምጠናል” ብለዋል።
የፕሮጀክቶቹ ስራዎች የመገጭን ግድብ ማጠናቀቅ የጎንደር ከተማን የውሃ አቅርቦት ማሻሻል እና የአዘዞ ጎንደር 11 ኪሎ ሜትር መንገድ ሥራ መፈፀም መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በዛሬ ጠዋቱ ግምገማ በመመስረት ስራዎቹ በመጪዎቹ ወራት በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የፕሮጀክቶቹ አስተዳደር ማሻሻያ እንዲደረግ መመሪያ መስጠታቸውንም አስታውቀዋል፡፡