Fana: At a Speed of Life!

ባንኩ ለአምራች ኢንዱስትሪው 30 ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 30 ቢሊየን ብር ለአምራች ኢንዱስትሪው ብድር መስጠቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎን ለጎን “የግል ኢንቨስትመንት እና አስቻይ ሁኔታዎች” በሚል የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባንኩ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ በዝቅተኛ ወለድ ብድር በመስጠት የዘርፉን ተዋንያን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ባንኩ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደነበር ገልጸው÷ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከነበረበት ችግር ማውጣት መቻሉን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ባንኩ በዓመት እስከ 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ እያገኘ መሆኑን፣ ካፒታሉ 38 ቢሊየን ብር መድረሱንና ለአንድ ፕሮጀክት እስከ 9 ቢሊየን ብር ማበደር የሚችልበት አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ 44 ቢሊየን ብር ብድር ማጽደቁን ገልጸው÷ ከዚህም 30 ቢሊየን የሚሆነው ለአምራች ዘርፉ የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው÷ንግድ ባንክ በከፍተኛ ሁኔታ አምራች ዘርፉን እየደገፈ የሚገኝ ተቋም ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ባንኩ አጠቃላይ ለብድር ከመደበው ካፒታል ውስጥ 50 በመቶውን ወይም 550 ቢሊየን ብር ለኢንዱስትሪዎች መስጠቱን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ 90 ነጥብ 6 በመቶው ብድር የረዥም ጊዜ ብድር መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.