አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪው መነቃቃቱን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ወዲህ የታየው የአምራች ኢንዱስትሪው መነቃቃት አበረታች መሆኑን ኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሽመልስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ክልላችንም አምራች ኢንዱስትሪውን እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ወስዶና በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶችና እድሎች ለይቶ መንቀሳቀሱ ለተጀመረው ንቅናቄ ጉልበት እየሆነው ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪው የኢንቨስትመንት ንቅናቄ ግልፅ ስትራቴጂና ግብ እንዳለው ጠቁመው÷ በዚሁ መሠረት ብዙ የሥራ እድሎችን በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እንዲሁም የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ረገድ ሰፊ ስራ በመከወን ላይ እንገኛለን፤ አበረታች ውጤቶችም ተመዝግቧል ነው ያሉት።
የተለያዩ የምክክር መድረኮችን በመፍጠር የአምራች ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር መቻሉንም አንስተዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት፣ የግንባታና የምርት ግብአቶች ማነቆዎች ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በውጤቱም ብዙ ኢንዱስትሪዎች በተነቃቃ ሁኔታ ወደ ምርት መመለሳቸውን ጠቁመው÷ በዚህ የስኬት ጉዞ፣ ከምንም በላይ የአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት ጨምሯል፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትም እየሰፋ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን እና ስለዘርፉ ያለው ግንዛቤም መሻሻል ማሳየቱን ገልጸው÷ ይህም የአምራች ኢንዱስትሪው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻውን እንዲያሳድግ አስችሎታል ነው ያሉት፡፡
ይህ ማለት ግን የዘርፉ ጉዞ በሚፈለገው ፍጥነት ላይ ደርሰናል ማለት አይደለም ያሉት አቶ ሽመልስ÷ በቀጣይ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን በመጠቀም በነባር በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ ያሚስተዋሉ ያልተቀረፉ ማነቆዎችን ለይተን ለመፍታት እንዲሁም ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የምንሰራ ይሆናል ሲሉ አመላክተዋል፡፡