የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቅርስ ምርምር ጉባዔ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቅርስ ምርምር ጉባዔ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በጉባዔው ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ጉባዔውን በይፋ ያስጀመሩት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ÷ ምድረ ቀደምት የሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን አውስተዋል፡፡
“በተለያዩ መንገዶች ተጠብቀዉ እዚህ የደረሱ ቅርሶችን እኛም ዘመናችንን በሚመጥን መልኩ መዝግበን፣ ተንከባክበን እና አልምተን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል” ብለዋል ።
ሚኒስትሯ አክለውም “ሀገራችን ካላት የቅርስ ብዛትና ዓይነት አንፃር መልማት የቻሉት ጥቂቶቹ ብቻ በመሆናቸውና ቅርሶችን ለቱሪዝም ልማት ባለመጠቀማችን ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ አጥታለች ” ነው ያሉት፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግስት ለቅርስ እንክብካቤ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ስራዎች መሰራታቸውንም አመላክተዋል ።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምርና እንክብካቤ የ80 አመታት ጉዞን የሚዳስሱ ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን÷ ከጉባዔው ጎንለጎን የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቅርሶች ዐውደ-ርዕይ የመክፈቻ ሥነ -ሥርዓትም ተካሂዷል ።
በምንተስኖት ሙሉጌታና አሸናፊ ሽብሩ