ባለስልጣኑ ከደረጃ በታች የሚያመርቱ የፕላስቲክ አምራቾች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከደረጃ በታች የሚያመርቱ የፕላስቲክ አምራቾች ከዛሬ ጀምሮ ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ ፋብሪካቸው እንደሚዘጋ የከተማው አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አሳስቧል።
ባለስልጣኑ በፕላስቲክ አጠቃቀምና አወጋገድ ዙሪያ ከፕላስቲክ አምራቾች፣ ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውሉ አምራቾች እና የፕላስቲክ ተኪ ምርቶችን ከሚያመርቱ አምራቾች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
የአዲስ አበባ አካባቢ ባለስልጣን ዋና አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ በመድረኩላይ እንዳሉት፥ ከደረጃ በታች እየተመረቱ የሚገኙ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ስለማይቻል አካባቢ ላይ ብክለትን በማስከተል ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።
የፕላስቲክ አምራቾች ደረጃቸውን የጠበቁ የፕላስቲክ ምርቶችን ሊያመርቱ እንደሚገባ አሳስበው፥ ከዛሬ ጀምሮም ከደረጃ በታች የሚያመርቱ አምራቾችን ባለስልጣኑ እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል፡፡
በሁለት ዓመት ውስጥም በአካባቢ ብክለት ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ በነበሩ 2 ሺህ 357 የተለያየ ምርት አምራች ፋብሪካዎች ላይ ላይ ርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ