ምክር ቤቱ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚያደርገውን ትብብር እንደሚያጠናክር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ መሳካት አስፈላጊውን እገዛና ትብብር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ የምክክር ሒደቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ሲያበረክት የቆየውን አስተዋጽኦ በማስመልከት ውይይት እያደረገ ይገኛል።
ከዚሁ መድረክ በተጓዳኝም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚያስረክቡ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል÷ ምክር ቤቱ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬት የበኩሉን በማበርከት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የምክር ቤቱ ድጋፍና አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዛሬው ዕለትም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡ እና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚያስረክቡ ጠቁመዋል።
በውይይት መድረኩ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።