Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት መቀላቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል ነው – አምባሳደር ምስጋኑ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል የምታደርገው ጥረት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ዋና አካል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለፁ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በዓለም የንግድ ድርጅት የአባልነት ክፍል ዳይሬክተር ከሆኑት ማይካ ኦሽካዋ ጋር ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጀት አባል የምትሆንበት ሂደት እንዲፋጠን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም አምባሳደር ምስጋኑ የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልፀው÷ ድርጅቱን ለመቀላቀል ያስቀመጣቸው ቴክኒካዊ ድርድሮች መጠናቀቃቸውን አንስተዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላለቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል መሆኑን ጠቅሰው÷ ሂደቱን ለማፋጠን ኢትዮጵያ የንግድና ፋይናንስ ዘርፍ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጓን አስረድተዋል፡፡

ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሆነችው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ የተቋሙን አቅም እንደሚያጠናክርም አስገንዝበዋል።

ዳይሬክተር ማይካ ኦሽካዋ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል የጀመረችውን ሂደት ለማፋጠን የድርጅቱ ሴክሬታሪያት አስፈላጊውን እገዛ እያደረገ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.