በግንባታው ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመከላከል መመሪያ ቁጥር 5 ጸደቀ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በግንባታው ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመከላከል መመሪያ ቁጥር 5 መጽደቁን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ጠቅላይ አቃቤ ህጓ በፌስ ቡክ ገጻቸው እንዳስታወቁት ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በተደረገው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ በግንባታው ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመከላከል፣ ዝግጁነትን ለማረጋገጥ እና ምላሽ አሠጣጥ ሁኔታዎችን ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 5 ጸድቋል።
የግንባታው ዘርፍ በሀገራችን እድገት ወሳኝ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል የከፈተ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኮቪድ 19 በዘርፉ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኝ ገልጸዋል።
በመሆኑም የግንባታው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትንና የግንባታ ቤተሰብን ጤንነትና ደህንነት ማስጠበቂያ እርምጃዎችን በአግባቡ በግንባታ ሳይቶችና በግንባታ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የማረጋገጥ ስራን መስራት በሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መደገፍ ተገቢ በመሆኑ መመሪያው መውጣቱን አስረድተዋል።
ዝርዝር ሁኔታው በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ይገለጻልም ብለዋል።