ዓለም አቀፍ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በአፍሪካ ለመጀመሪያው ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ ላይ ከ50 በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢሊባቦር ቡኖ÷ ጉባዔው በኢትዮጵያ መካሄዱ ከተሳታፊዎች የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም የሚያስችል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የድንገተኛ አደጋ ሕክምናን ለማዳረስ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ታስቦ መዘጋጀቱን የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ሰርጀሪ ዲፓርትመንት ተወካይ ሪቻርድ ጋርድነር ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የጤና አጠባበቅ ውጤቶችን ማሻሻል ላይ በመወያየት እንዲሁም ዕውቀትና ልምድ እንዲለዋወጡ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።