የፋና ላምሮት ምዕራፍ 17 ውድድር ነገ አዳዲስ ነገሮችን አካትቶ ይጀምራል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአስደናቂው 4ኛው የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ የፍፃሜ ውድድር በኋላ እረፍት ላይ የቆየው ፋና ላምሮት የባለተሰጥኦ ድምፃውያን ውድድር ነገ በአዳዲስ ነገሮች በምዕራፍ 17 ውድድሩ ይመለሳል።
ባለፉት ሁለት ሣምንታት 16ቱ ተወዳዳሪዎች ዳኞች በሌሉበት ከእናንተ ተመልካቾችና ከውድድሩ ጋር ትውውቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ከሌላው ጊዜ በተለየ አዳዲስ ጉዳዮችን ይዞ የሚመለሰው 17ኛው ምዕራፍ የፋና ላምሮት የባለተሰጥኦ ድምፃውያን ውድድር በነገው ዕለት ከ6 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ስርጭት ይጀምራል።
ምዕራፉ የተወዳዳሪዎችን ቁጥር ጨምሮ 16 ተወዳዳሪዎች በሁለት ምድብ ተከፍለው ለ13 ሣምንታት የሚወዳደሩ ሲሆን፥ ነገ የምድብ አንድ ተወዳዳሪዎች በሁለት ዙር በመረጧቸው ሙዚቃዎች ይወዳደራሉ።
የምድብ አንድ ተወዳዳሪዎች ፥ ናሆም ነጋሽ፣ ጴጥሮስ ማስረሻ፣ ፀጋሰጠኝ ሰይፉ፣ ኤርሚያስ ዳኛቸው፣ ትዕግስት አንተነህ፣ ጌታነው ስመኘው፣ ዘላለም ፀጋዬ እና ዝንታለም ባየህ ናቸው።
በሙዚቃ ባለሙያዎች እና በተመልካቾች የጽሁፍ መልዕክት (ኤስ ኤም ኤስ) የሚዳኘው የፋና ላምሮት የድምፃውያን ውድድርን በፋና ቴሌቭዥን፣ በፋና የፌስቡክ እና የቴሌግራም ገጾች ጨምሮ በ www.fanabc.com ከ6 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ሥርጭት እንዲከታተሉ ይጋበዛሉ፡፡
በተጨማሪም በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተወዳዳሪዎችን ኮድ በመላክ እየተዝናኑ መደገፍ ይችላሉ።
በለምለም ዮሐንስ