2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ሀገርን ጽዱና ውብ እንደሚያደርጋት ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ጥሪውን ተከትለው በኢትዮጵያ ያሉ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ሀገሪቱን ጽዱና ውበ የሚያደርጋት እንደሆነ ተናግሩ።
የዳያስፖራ አባላቱ ንቅናቄው በሌላው ዓለም በተመለከቱት ቁጥር ለሀገራቸው ሲመኙ የኖሩትን እውን ለማድረግ እድል የሰጣቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ተገንብተው የከተማዋን ገጽታ ከፍ በማድረግ የሚታይ ውበትን ካላበሷት እና እያላበሷት ካሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለከተማዋ ተጨማሪ ጽዳት እና ውበት የሚያላብስ ነውም ብለዋል።
የሀገርን ጥሪ ተቀብለው የመጡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ንቅናቄውን መቀላቀላቸውን ገልፀው ፥ ሌሎችም ንቅናቄውን እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል።
አክለውም ከባድ እና ሩቅ የሚመስላቸውን ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶችን በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በህዝብ ተሳትፎ እውን ሊሆኑ መቃረቡ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
በመራዖል ከድር