Fana: At a Speed of Life!

የ2017 በጀት ስሚ መርሀ-ግብር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 በጀት ስሚ መርሀ-ግብር የገንዝብ፣ የማዕድንና ነዳጅ እንዲሁም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚቀጥለው ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በመወያየት ተጠናቀቀ፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር የበጀት ስሚ ውይይትን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ÷ የማዕድና እና ነዳጅ ዘርፍ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ፈጣን ውጤት ሊገኝበት የሚችል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ያላት ሀብት ውስን በመሆኑ ተቋሙ የሚመደብለትን መደበኛ ካፒታል በጀት በአግባቡና በቁጠባ ስራ ላይ ማዋል እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡

በተጠሪ ተቋማት የቀረበው የተሸከርካሪ አቅርቦት ችግር በማዕከል ደረጃ የሚፈታ መሆኑንና ተቋማት ወጪ ለመቆጠብ ተብሎ ለሁለተኛ ወገን የሚያስተላልፏቸው ስራዎች ከፍተኛ ወጪ እየጠየቁ ስለሆነ መስተካከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር በ2017 በጀት ዓመት በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ መስራት እንዳለበት ገልጸው፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የኮርፖሬት አስተዳደር ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የበጀት ስሚ መርሀግብርን የመሩት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የቀረበው የበጀት ፍላጎት ከተሠጠው ጣሪያ ብዙም ያልራቀና የሚያግባባ ነው ብለዋል፡፡

የ2017 በጀት ስሚ መርሀ-ግብር የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ውስጥ ተቋማት ከገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጣቸው የበጀት ጣሪያና የማስተካከያ ሀሳብ መሰረት የበጀት እቅዳቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.