ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በትኩረት እየሰራች ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን እና መዋቅራዊ ሽግግርን በማረጋጋጥ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በትኩረት እየሰራች ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በአፋር ክልል የግብርና ሽግግር ፍኖተ-ካርታ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል።
ፍኖተ-ካርታውን ግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
በመድረኩ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን እና መዋቅራዊ ሽግግርን በማረጋጋጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ከውጪ የሚገባ ምርትን የሚተካና ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ከማምረት ባለፈ ግብርናውን ከበሬ ትከሻ በማውረድ በሜካናይዜሽን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
አክለውም ፥ ግብርናውን ከክረምት ዝናብ ጥበቃ በማላቀቅ የግብርና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያነሱት።
ለዚህም የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታዎች ተሰናድተው በተለያዩ ክልሎች ተግባራዊ እየሆኑ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፥ ዛሬ በአፋር ክልል ይፋ የሆነው ፍኖተ-ካርታም የዚያው አካል ነው ብለዋል።
አፋር ክልል ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ውሃና መሬትን ማገናኘት እንደሚገባ ገልጸው ፥ በፍኖተ -ካርታውም በዋናነት መኖ በስፋት ማምረት ፣ የመስኖ ስንዴን ማልማትና አትክልትና ፍራፍሬ ላይ አበረታች ውጤት ማምጣት የሚያስችል እቅድ ተይዟል ነው ያሉት።
አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ፥ ክልሉ ሰፊ የግብርና እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ ያለው በመሆኑ ሃብቱን ተጠቅሞ የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የግብርና ሽግግር ፍኖተ-ካርታው ወሳኝ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የግብርና ሽግግር ፍኖተካርታ ውጤታማ እንዲሆንም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ