የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ወራት በክልሉ በየዘርፉ እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች ሥራዎችን ማስቀጠልና ክፍተቶችን ለማረም በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በዋናነትም ብቁ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ ይገባል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ከማጠናቀቅ አንፃርም ባለፉት ወራት የተከናወኑ አበረታች ስራዎች ማጠናከር እንዲሁም የተጀመሩ የቱሪዝም ልማት ስራዎች እንዲጠናከሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የሌማት ቱርፋት፣ የከተማ ግብርና ስራዎችን ማጠናከር እንዲሁም የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችም የላቀ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ የግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር እና የህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ስርዓት የማስያዝ ስራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ የማስቀጠል እና የማዕድን ሃብትን በአግባቡ የማስተዳደር ስራ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
የከተማ ጽዳትና ውበት ስራን የማጠናከር እንዲሁም ለእግረኛ መንገድ አገልግሎት እንዲውሉ ክፍት የተደረጉ ቦታዎችን ለእግረኛ ምቹ የማድረግ ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው መጥቀሳቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍና ብልሹ አሰራር የመከላከል እንዲሁም የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያን ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍም በጥናት የተደገፈ ስራ እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ነው የገለፁት።