የማዕድን ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የማዕድን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር ሃብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።
በክልሉ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የማዕድን ሃብት ልማት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
አቶ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ ያለውን የማዕድን ሃብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ ከልማቱ አንስቱ በዝውውሩ ላይ የሚስተዋሉ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር ሃብቱን በአግባቡ ለማልማት የተጀመረው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድርና የማዕድን ዘርፍ ቦርድ ሰብሳቢ ቴንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው÷በክልሉ ሰፊ የማዕድን ሃብት ቢኖረም በሚፈለገው መጠን አልምቶ ከመጠቀም አንፃር ውስንነቶች አሉ ብለዋል።
በመሆኑም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የማዕድን ሃብት ልማትን በማጠናከር ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረውን አስተዋፅኦ ለማጎልበት በቁርጠኝነት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተለይም በማዕድን ሀብት ልማቱ ላይ ከክልል እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያለውን አደረጃጀት ወጥ በማድረግ ሀብቱን ከብክነት ለመታደግ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አኳታ ቻም÷ በስራ ዘመኑ የኮንስትራክሽን ማዕድን ሀብት ልማት ላይ ለመሰማራት ፍቃድ ለሚጠይቁ ባለሃብቶች ፈቃድ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የማዕድን ሀብቱን ከህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ለመታደግም እንደ ክልል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።