የሀገር ውስጥ ዜና

ቢቢሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በተያያዘ ተናግረውታል ብሎ ላወጣው ዘገባ ይቅርታ ጠየቀ

By Tibebu Kebede

June 13, 2020

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታንያው የዜና አውታር ቢቢሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በተያያዘ ብለውታል በሚል ላወጣው ዘገባ ይቅርታ ጠየቀ።

ባለፈው ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ቢቢሲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሱዳን እና ግብጽን መለመን ሰልችቷታል” ብለዋል በሚል በቀጥታ ስርጭት ዘገባው አስነብቦ ነበር።

ይሁን እንጅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተገለጸበት ዘገባ ስህተት እንደነበር ቢቢሲ አስታውቋል።

ሃሳቡ በስህተት ከመገለጹ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ስህተትም ይቅርታ ጠይቋል፤ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው ስህተትም በሁሉም የጣቢያው ገጾች ላይ መስተካከላቸውንም አስታውሷል።