የጠቅላይ ሚኒስትር ተጠሪ ተቋማት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ተቋማት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
በግምገማው ተጠሪ ተቋማት ሀገራዊ የልማትና የለውጥ ኢኒሼቲቮችን ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ በሚሆን መልኩ እየፈጸሙበት ያለው ሂደት በዝርዝር እንደሚገመገም ተጠቁሟል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በግምገማው የዘጠኝ ወራት ዝርዝር አፈጻጸምን በጥልቀት በመዳሰስ ለቀጣይ ተልዕኮ መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ተጠሪ ተቋማት ኢትዮጵያን ወደተሻለ ሁለንተናዊ ምዕራፍ ለማሻገር እየተተገበሩ የሚገኙ ሀገራዊ ዕቅዶችን ከማሳካት አንፃር አርዓያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለአብነትም መንግሥት አገልግሎትና መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል የጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለማሳካት በቀዳሚነት እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል።
እንደ ሀገር ወደ ዲጅታላይዜሽን ለሚደረገው ሽግግር የተጀመሩ ሥራዎችን በውጤት መምራት ይጠበቃል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።