በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳካት የሚያስችል አመላካች ውጤት ተመዝግቧል- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የተተነበየውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳካት የሚያስችል አመላካች ውጤት መመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ÷ ባለፉት 9 ወራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች የተተነበየውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማሳካት እንደሚቻል አመላክቷል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በሰብሎች ልማት ከ100 ሚሊየን ኩንታል በላይ መገኘቱን ጠቅሰው÷ከዚህ ውስጥ ስንዴ ከ80 ሚሊየን ኩንታል በላይ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሩዝ ምርት 38 ሚሊየን ኩንታል፣ ወተት 2 ቢሊየን ሊትር፣ እንቁላል 2 ቢሊየን እና ስጋ 200 ሺህ ቶን መመረቱን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም አፈጻጸም 56 በመቶ መድረሱንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
በአገልግሎት ዘርፍ፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪስት ፍሰትና በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት 374 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የተናገሩት ሚኒስትሯ÷ ከወጪ አንጻርም 495 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ትልቁን ወጪ የሚሸፍነው የካፒታል ወጪ እንደሆነ እና ይህም 15 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከሸቀጦች የወጪ ንግድ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር፣ ከአገልግሎት ወጪ ንግድ ደግሞ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ ለማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እድገት መታየቱን ተከትሎ የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ትንበያው እውን እንደሚሆን አመልክተዋል።
በታሪኩ ለገሰ