Fana: At a Speed of Life!

ቃል በገባነው መሰረት የተወሰኑ መንገዶችን አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል – ከንቲባ አዳነች

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቃል በገባነው መሰረት ከጥቃቅን ሥራዎች በስተቀር የተወሰኑ መንገዶችን አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነቸ አቤቤ ገለፁ፡፡

የአሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መገምገማቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ቃል በገባነው መሰረት ከጥቃቅን ሥራዎች በስተቀር የተወሰኑ መንገዶችን ሥራ አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ለአብነትም÷ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ አድዋ ድል መታሰቢያ፤ ከደጎል እስከ ቀይ ባህር ኮንዶሚኒየም፤ ከአራት ኪሎ እስከ ቅ/ማርያም መገንጠያ፤ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ሳርቤት ያሉትን መንገዶች ተቅሰዋል፡፡

ቀሪዎቹንም በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሳምንቱን ሙሉ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ስራው ከ48 ኪሎ ሜትር በላይ የተሽከርካሪ የመንገድ ልማት፣ 4 የመሬት ውስጥ የእግረኛ መንገዶች፣ 96 ኪሎ ሜትር ሰፋፊ የእግረኛና 100 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገዶች፣ 5 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ፣ 48 የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሳልጡ የአውቶቡስ እና የታክሲ ተርሚናሎችንና መጫኛ ማውረጃ ስፍራዎች፣ በጥቅሉ ከ 240 ኪሎ ሙትር በላይ የሚሆን የመንገድ እና ተያያዥ መሰረተ ልማት፤ 70 የከተማ ውበትን የሚጨምሩ የህዝብ መናፈሻ ስፍራዎች እየገነባን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ፋውንቴኖችና የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመዝናኛና የመናፈሻ ስፍራዎች፣ የልጆች መጫዎቻና የህዝብ ፕላዛዎች፣ 120 የሚሆኑ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የከተማዋን ማዘጋጃዊ አገልግሎቶችን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ የፍሳሽ ማስተላለፊያዎች፣ ከተማችንን የሚመጥኑ የደህንነት ካሜራዎች፣ የብልህትራንስፖርት ስርዓት በመሬት ውስጥ የመዘርጋት ስራ ፣ ከ400 በላይ ህንጻዎች እንዲታደሱ የማድረግ እንዲሁም የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ የቀለምና የመብራት ስራዎች እና ሌሎች በርካታ ግንባታዎች በመከናወን ላይ እንደሚጓም አብራርተዋል፡፡

የግንባታ ስራው ሲጠናቀቅም አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም እየጨመረ የመጣውን የመዲናዋን ዓለምአቀፍ የስበት ማዕከልነት በማሳደግ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሰነቀውን ራዕይ በማሳካት ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.