የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም የአውደ ጥናት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ50 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም አውደ ጥናት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ ቴሌኮም ህብረት አስተባባሪነት የተዘጋጀው መድረኩ በአፍሪካዊያን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ የብሔራዊ የፍሪኩዌንሲ ሃብት ቀልጣፋና ፍትሃዊ ተደራሽነትን እንዲኖር ከዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት (ITU) ጋር በቅርበት መስራት አስፈለላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዲጂታል ልማትና ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁርጠኛ ነች ያሉት ሚኒስትሩ÷ ቴክኖሎጂ በአህጉራችን እድገት ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና በመገንዘብ ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ ልማትና እድገት አጋዥ መስመሮችን ለማሳለጥ እንተጋለን ብለዋል።
አውደ ጥናቱ በስፔክትረም አስተዳደር ባለስልጣናት መካከል ትብብርና የእውቀት ልውውጥን ለማጎልበት፣ የስፔክትረም አጠቃቀምን ለማመቻቸት፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና በየሀገሮቻችን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መበልፀግ አጋዥ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት (ITU) ተወካይ ዣንዣክ ማሲማ በበኩላቸው÷ አውደ ጥናቱ በአፍሪካ የሚስተዋለውን የሬድዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም ክፍተት በመሙላት የአፍሪካን ግኑኝነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን መናገራቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡