የፋይናንስ ስርዓቱን ጤናማነት ለማስጠበቅ የመንግስት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል-ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተልዕኮ ስኬት እንዲሁም የፋይናንስ ስርዓቱን ጤናማነት ለማስጠበቅ የመንግስት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አሁን ያለበትን ቁመና ጎብኝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ ዕድገት እንዲኖረው እና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ የዲጂታል አሰራሮችን ማዘመን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊና የራስ አስመስሎ የማቅረብና የመጠቀም ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለፉት ጥቂት አመታት ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡
ከሪፎርም በኋላ ተቋሙ አሁን የደረሰበት ደረጃ አበረታች እና ወሳኝ ማነቆዎችን መሻገሩን መረዳት ችለናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ትኩረት የሚሹና ጥልቅ ስራ በሚጠይቁ ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያታቸውን ገልጸዋል ።
የተቋሙ የተልዕኮ ስኬት እንዲሁም የፋይናንስ ስርዓቱን ጤናማነት ለማስጠበቅ የመንግስት ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡