ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ከሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ማሕሙድ ድሪር ገለጹ፡፡
ኮሚሽኑ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
ኮሚሽነር አምባሳደር ማሕሙድ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክክሩ እንዲሳካ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው÷ ለዚህም ኮሚሽኑ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመቀራረብ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
መድረኩም ግንኙነቱን የበለጠ በማጠንከር በቀጣይ የሚኖሩ የምክክር ሂደቶችን በስኬት ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለግማሽ ቀን በሚቆየው መድረክ ላይ መገናኛ ብዙኃን ምክክሩን በተመለከተ በሠሯቸው ሥራዎች ላይ የዳሰሳ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡