ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ ሲሸጡ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ መታወቂያና ስሞችን በመጠቀም የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን አውጥተው ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ በመሸጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ሥድስት ተጠርጣሪዎች ተያዙ፡፡
ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቤት በመከራየት በሀሰተኛ መታወቂያ በወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ግብይት ሳይኖር ግብይት ያለ በማስመሰል ደረሰኝ ሲሸጡ ነበር ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ለማውጣት በንግድ ስራ ላይ ያልተሰማሩና በአነስተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ ግለሰቦችን በገንዘብ አታለው እውነተኛ ስማቸውን እንዲቀይሩ በማግባባት የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽንን ጨምሮ የንግድ ምዝገባ ፍቃድና የንግድ ፈቃድ መለያ ቁጥር እንዲያወጡ አድርገዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከእነዚህ ግለሰቦች ውክልና በመውሰድ መመዝገቢያ ማሽኑ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ከሁለት ዓመት በላይ ደረሰኝ በመሸጥ ሲጠቀሙበት እንደነበር በምርመራ ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ባደረገው ጥናትና ክትትል በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ነው ተብሏል፡፡
ለወንጀሉ መፈፀሚያ የሚጠቀሙባቸው የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች፣ ኮምፒውተሮች፣ ስካነር፣ ሃሰተኛ ማህተሞች፣ የእጅ በእጅ የሽያጭ ደረሰኝ እና ሌሎች የተለያዩ ሰነዶች መያዛቸው መገለጹን የአዲስ አበባ ፖሊስ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታወቋል፡፡