የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው – ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋትን በመንከባከብ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኢንስቲትዩቱ የደን እና ግጦሽ ዕጽዋት ምርምር ሥራ አስፈጻሚ አበራ ስዩም÷ ኢንስቲትዩቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ለሀገር በቀል ዕፅዋት ትኩረት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገር በቀል ዕፅዋትን መትከል የአካባቢ ሥነ -ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋቶች መልሰው እንዲያገግሙ ሰፊ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለብዝሃ-ሕይወት ጥበቃ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸው÷ ይህን ለማጠናከር ተቋሙ እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕጽዋትን በመንከባከብ ላይ መሆኑንና በሀገር በቀል ለመተካት ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ሀገር በቀል የሆኑ ችግኞችን ኮሶ ፣ብርብራ ፣የሀበሻ ጽድ፣ ቀርቀሃንና መሰል የደን ተክሎችን ጨምሮ ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አቶ አበራ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የተዘጋጁት ችግኞች በሙሉ ሀገር በቀል መሆናቸውን ገልጸው ÷በዘንድሮ በአረንጓዴ አሻራ ከጥላ ዛፍ በተጨማሪ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ፓፓያ እና አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች ፍራፍሬዎችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል ፡፡