ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ለማሳካት መሰረት የምንጥልበት ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ለማሳካት መሰረት የምንጥልበት ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
‘ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዐላዊነትና ክብር’ በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ የሚመከርበት መድረክ በዛሬው እለት በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት መካሄድ ጀምሯል።
በመርሀ ግብሩ አቶ አደም ፋራህ÷ እንደ ሀገር ከተረጂነት እና ከልመና መላቀቅ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
ከተረጂነት አስተሳሰብ ሳይላቀቁ ሉዐላዊነት እና ብሔራዊ ክብርን በሙሉዕነት መጎናፀፍ እንደማይቻልና ለዚህም በቁርጠኝነት መነሳት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት በአግባቡ አቀናጅቶ በመጠቀም እና ለብልፅግና በማዋል የተረጂዎችን ቁጥር መቀነስ፣ ቀስ በቀስም ከተረጂነት ሙሉ ለሙሉ ማላቀቅ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ለዚህም ብቸኛው መፍትሄ ምርታማነትን በሁሉም ደረጃ ማሳደግ መቻል እንደሆነ ማንሳታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ የተረጂነት አስተሳሰብ እንደ ሀገር ሊፈጥረው የሚችለውን ቀውስ በውል በመረዳት ጉዳዩን ከስሩ ለመፍታት ሰፋፊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በተለይም ምርታማነትን አሳድጎ ዘላቂ እልባት ለማምጣት እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ የተደረጉ የሌማት ትሩፋትን የመሰሉ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እንዳስመዘገቡ ጠቅሰዋል።
በላባችን እና በጥረታችን ከተረጂነት በመላቀቅ ብልፅግናን የማረጋገጥ ምዕራፍ መጀመር እንዳለብንና ይህንን ማሳካትም ለሁለተኛው የአርበኝነት ምዕራፍ ጠንካራ መሰረት መጣል እንደሆነ ገልፀዋል።