Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ  በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ካቢኔው ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ቀለብ ማሻሻያ ላይ ተወያይቷል።

በዚሁ ውይይት በክልሉ የሚገኙ አሶሳ፣ ካማሽ እና መተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ  የታራሚዎች  የቀለብ ማሻሻያን አስመልክቶ ቀደም ሲል  ሲቀርብ የነበረው የቀለብ ተመን ሳይሻሻል የቆየ መሆኑ ተነስቷል፡፡

ካቢኔው በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በአሁኑ ነባራዊ የገበያ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በአዲሱ በጀት ዓመት ማሻሻያው ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል።

ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን ከማነፅ በተጨማሪ ከመንግስት ጠባቂነት ተላቀው የውስጥ ገቢያቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ካቢኔው አቅጣጫ አስቀምጧል።

በሌላ በኩል በከተሞች የሚከናወኑ ኢንቨስትመን ስራዎች ለከተሞች እድገት እና ለተክኖሎጂ ሽግግር አስተዋፅኦ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ካቢኔው መግለፁን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች ደንብና መመሪያውን ተከትለው እንዲቀርቡና ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ካብኔው አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.