የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ለውጥ አምጥተዋል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ለውጥ ማምጣታቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
በክልሉ ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሀ ግብር በዛሬው ዕለት ሲካሄድ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የክልሉን ገቢ ለማሳደግ የህግ ማዕቀፍ የማሻሻል፣ ግብር የሚሰውሩ አካላትን ህጋዊ መስመር የማስያዝ፣ የኮንትሮ ባንድ እንቅስቃሴዎችን የመከላከልና ሌሎች የማሻሻያ ስራዎች መከናዎናቸውን ገልጸዋል።
የማሻሻያ እርምጃዎቹ አበረታች ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸው፤ በታማኝነት ግብር የሚከፍሉ ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችን አመስግነዋል።
እናንተ ባገለገላችሁን ልክ እኛም ልናገለግላችሁ እንሰራለን በማለት ገልጸው፤ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ቱሉ በበኩላቸው የሚሰበሰበው የታክስ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለአብነትም በ2011 ዓ.ም 198 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ ባለፈው በጀት ዓመት 442 ቢሊየን ብር ያህል መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ በ10 ወራት ውስጥ 425 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡንም ጨምረው ገልጸዋል።
እየተሰበሰበ ያለው ገቢ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ በመሆኑ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመንና በቴክሎጂ የታገዘ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በተስፋዬ ምሬሳ