Fana: At a Speed of Life!

የሥራ ገበያ ትስስርና ድጋፍ ፕሮጀክት ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጣልያን ዓለም አቀፍ ትብብር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ተግባራዊ የሚያደርገው የሥራ ገበያ ትስስርና ድጋፍ ፕሮግራም ላይ ውይይት ተደረገ፡፡

በውይይቱ የሥራ ገበያ ትስስርና ድጋፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረግባቸው የአማራ፣ የሲዳማና የኦሮሚያ ክልሎች ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት  ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ  የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ÷ ፕሮጀክቱ  በሥራ ሥምሪት አገልግሎት ማዕከላት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት የማሻሻልና ተደራሽነታቸውን የማስፋት ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የሥራ ሥምሪት አገልግሎት ማዕከላትን ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ፣ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ከግል ንግድ ድርጅቶች ጋር የሚያስተሳስር ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም ክልሎች መሰል ዓላማ ያላቸውን ፕሮጀክቶች አቀናጅተው በውጤታማነት መምራት እንደሚኖርባቸው ማሳሰባቸውን ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሥራ ገበያ ትስስርና ድጋፍ ፕሮጀክት በቡሬ፣ በቡልቡላ፣ በጅማ እና በይርጋዓለም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ በሚገኙ 16 ከተሞች ላይ ለሚኖሩ ዜጎች የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.