አንቶኒዮ ጉተሬዝ አፍሪካ በዓለም ሰላምና ደህንነት ያላትን አስተዋጽዖ እንድታበረክት ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአፍሪካ አህጉር በዓለም ሰላም እና ደህንነት ሚናዋን እንድትጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ የአፍሪካን ተሳትፎ እና አመራር በዓለም አቀፍ የሰላም እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ማካተት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ዘዴዎች የተነደፉት በወቅቱ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛትን ሰንሰለት በመጣል ላይ በነበሩበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለም ቢለወጥም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን ባሉበት ናቸው ብለዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ዓለም አቀፋዊ የደህንነት እና የልማት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን ሚና አስመልክቶ እንዳሉት፥ “በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ምክር ቤት ጭምር በድርድር ጠረጴዛ ላይ መቀመጫ መከልከላቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ አፍሪካ ትኩረት እንዳጣች ገልጸዋል።
በመሆኑም አፍሪካ በዓለም ሰላም እና ደህንነት ድምጿን ማሰማት እንደሚገባት ገልጸው፥ ይህንን እውን ማድረግ የሚቻለው የአፍሪካ ሀገራት በእኩልነት በዓለም አቀፍ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ መሳተፍ ሲችሉ እንደሆነ አስረድተዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት አናሳ የሆነውን የአፍሪካን ቋሚ ውክልና ማስተካከል እንዲሁም የእዳ አያያዝን ማሻሻልን ጨምሮ የዓለም የገንዘብ ስርዓት መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ያሉ ግጭቶች አብቅተው አህጉሪቷ ሰላም ማግኘት አለባት ማለታቸውን የዘገበው ዢኑዋ ነው፡፡
የተመድ የአፍሪካን ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው አንስተው፥ ይህም በአፍሪካ ህብረት ዋና ትኩረት በሆነው የጠብመንጃ እንቅስቃሴን በማስወገድ እንደሆነ አንስተዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ግጭቶች ከመባባሳቸው በፊት ለማርገብ፣ ከተከሰቱም በብቃት ለመቆጣጠር እና መፍትሄ ሲያገኙም ደግሞ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።